Phone: +251 582230475
Email: drptc2001@gmail.com
Facebook Telegram YouTube TikTok

የዱርቤቴ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ አከናወነ።

July 17, 2026
የዱርቤቴ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ አከናወነ።
የዱርቤቴ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ አከናወነ።

የዱርቤቴ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በ2018 በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ ያቀዳቸውን የሥራ እቅዶችና ፕሮግራሞች ምን ያህል እንደተፈጸሙ ለመገምገም የዓመቱን የሥራ አፈጻጸም ግምገማ አካሂዷል። በግምገማው የተገኙ ውጤቶች፣ የታዩ ጥንካሬዎች፣ ያሉ ክፍተቶች እና ለቀጣይ ጊዜ ሊወሰዱ የሚገቡ የማሻሻያ እርምጃዎች በስፋት ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የበጀት ዓመቱን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት የኮሌጁ ዕቅድና በጀት ባለሙያ አቶ አታላይ ገበየሁ ያቀረቡ ሲሆን፣ በመድረኩ ላይ ሁሉም የኮሌጁ አሰልጣኞችና አስተዳደር ሠራተኞች በንቃት ተሳትፈው በቀረበው ሪፖርት ላይ ሰፊ ውይይት አካሂደዋል።

በሪፖርቱ ውስጥ ኮሌጁ የውስጥ ገቢውን ለማሳደግ በተለያዩ የግብርና ልማት ሥራዎች ያከናወናቸው ተግባራትና በሂደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች በጥልቀት ተገምግመዋል። እነዚህ ሥራዎች ኮሌጁ ራሱን በራሱ አቅም የሚደግፍ እና ዘላቂ የገቢ ምንጭ የሚፈጥር ተቋም ለመሆን እያደረገው ያለውን ጥረት ያሳያሉ።

በተጨማሪም ኮሌጁ በ2018 በጀት ዓመት ውስጥ ISO 21001:2025/EOMS የትምህርት ድርጅቶች አስተዳደር ሥርዓትን በተሳካ ሁኔታ ለመዘርጋት በቂ በጀትና የሰው ኃይል በመመደብ የሥርዓቱን መስፈርቶች በመተግበር ለብቃት ማረጋገጫ የሚያበቃ ውጤት ማስመዝገቡም በሪፖርቱ ላይ በጎ ስኬት እንደሆነ ተገልጿል።

በውይይቱ ወቅት ተሳታፊዎች ያቀረቧቸው ጥያቄዎች፣ ሀሳቦችና ገንቢ አስተያየቶች በኮሌጁ ከፍተኛ አመራሮች በበቂ ማብራሪያ የተመለሱ ሲሆን፣ የግምገማው ዋና ዓላማ የተገኙትን ውጤቶች ማጠናከር፣ የታዩ ክፍተቶችን በማሻሻል በቀጣይ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገብ መሆኑ ተጠቅሷል።

በማጠቃለያውም በተያዘው የክረምት ወቅት የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች፣ የበጎ አድራጎት እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ተግባራት በቅንጅትና በከፍተኛ ትኩረት እንዲፈጸሙ አቅጣጫ ተሰጥቷል። ኮሌጁም የተቋሙን ጥራት፣ ተጠያቂነትና ቀጣይነት ያለው ልማት ለማረጋገጥ ከሠራተኞች፣ ከባለድርሻ አካላትና ከማኅበረሰቡ ጋር በመተባበር ሥራውን በብርቱ ቁርጠኝነት እንደሚቀጥል ተገልጿል

ዱርቤቴ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ
የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን
ሀምሌ 09/2018 ዓ.ም
ዱርቤቴ
Website developed by Mebtu : 0912705043